የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በማርሻል ግራዚያኒ ላይ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃትና የአርበኛነት ተጋድሎ ሲነሳ ቀድመው የሚታወሱት የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ተወላጆቹ አብርሃ ደሞጭና ሞገስ አስገዶም፤ ግፋ ካለም የሐረርጌው አማራ ሰምዖን አደፍርስ ብቻ ናቸው። በተለይም በዘመነ ደርግ ሻዕብያና ጀብሀ የተባሉ ተገንጣዮችን ትርክት በፕሮፓጋንዳ ለመብለጥ ሲባል የአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ስም የኤርትራ ተወላጆች ለኢትዮጵያዊነታቸው መስዕዋትነት የከፈሉ መሆናቸውን ለማሳየት እንደ አብነት እየተደጋገመ በየ መድረኩ ይወሳ ነበር። እርግጥ ነው እልቆ ቢስ የባሕረ ነጋሽ ልጆች ለኢትዮጵያዊነታቸው መስዕዋትነት ከፍለዋል። በዚህ ረገድ የጥቁር አንበሳው ጠቅላይ አዛዥ ሰማዕቱ ሌ/ኮሎኔል በላይ ኃይለአብ ቀዳዊው ተጠቃሽ ነው። ሆኖ ግን በደርግ ዘመን እንደዋዛ የተጀመረው እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን የካቲት 12 በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን ጥቃት የመሩና ያቀናበሩ የተደረጉበት ታሪክ በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ ያመነጩት፣ የመሩትና እቅዱን ያወጡት መታሰቢያ የታሪኩ ዋና ባለቤት የሆኑትን አርበኛ ውለታ የሚያስረሳ ስለሆነ መስተካከል ይኖርበታል። በማርሻል ግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን ኦፕሬሽን የጠነሰሱት፣ ለዚህ ኦፕሬሽን የማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ኦፊሰር የነበረውን አብርሃ ደሞጭና የግራዚያኒ አስተርጓሚ የነበረውን ሞገስ አስገዶምን የመለመሉት፤ ጥቃቱን እንዲፈጽሙ የተመለመሉት እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ ለዋሉት ውለታ የሚገባቸውን ለመክፈል ያሳመኑትና ከአዲስ አበባ ተሰውረው ወደ ሱዳን የሚሄዱበትን እቅድም ያወጡት በወቅቱ በነበራቸው ሥልጣን በጅሮንድ ኋላ ላይ በደረሱበት ማዕረግ ደግሞ ደጃዝማች የነበሩት ጀግናው አርበኛ ለጥ ይበሉ ገብሬ ናቸው። ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመርሐ ቤቴ አውራጃ አፍቀራ አምባ ማናለሽ ቀበሌ በ1885 ዓ.ም. የተወለዱ ሲሆን ከጥሊያን ወረራ በፊት የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በጅሮንድ ነበሩ። በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ኦፕሬሽር የመሩት ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ የግድያ ሙከራውን ያቀናበሩት ጀኔቭ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በግራዚያኒ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ ባስተላለፉላቸው ትዕዛዝ መሰረት ነው። እደግመዋለሁ! በማርሻል ግራዚያኒ ላይ ቦንብ የመጣልና ግራዚያኒን የመግደል ሐሳብ የተጠነሰሰው በንጉሠ ነገሥቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው! ከማይጨው ሽንፈት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ጀኔቭ ሄደው የኢትዮጵያውያንን አቤቱታ በመንግሥታቱ ማኅበር ፊት በየጊዜው እየቀረቡ ለማሰማት እንዲችሉ 15 የንጉሡ ረዳቶች፣ አገረ ገዢዎችና ሚኒስትሮች በጉባኤ ወሰኑ በሗላ ንጉሡ ጀኔቭ አቅንተው (በተለይም ፋሽስት ጣሊያን አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ) የገጠማቸው ትልቁ ፈተና፣ ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ስለተቆጣጠረች የመንግሥታቱ ማኅበር ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ወንበር ለጥሊያን ተላልፎ መሰጠት አለበት የሚለው የአባል ሀገራቱ ውሳኔ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ በሊግ ኦፍ ኔሽን የነበራት የአባልነት ወንበር ለፋሽስቶቹ ተላልፎ እንዳይሰጥ ለማድረግ ንጉሠ ነገሥቱ የነበራቸው አንድ አማራጭ አዲስ አበባን የተቆጣጠረውን የፋሽስት መሪ በመግደል የኢትዮጵያ አርበኞች አዲስ አበባን መልሰው ለመያዝ በመዋጋት ላይ መኾናቸውን ለማኅበሩ በማሳወቅና በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ ሳይኾን በዋና ከተማዋ በአዲስ አበባ ውስጥም አርበኞች ትግል ላይ እንደኾኑ ጥሊያን ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ እየገዛች አለመኾኗን ማሳየት ነበረባቸው። ባጭሩ ንጉሠ ነገሥቱ በዋና ከተማቸው ላይ እንዲደረግ ያሰቡትን ጉልህ ተጋድሎ ለዓለም በማሳየት ኢትዮጵያ በጀኔቭ የነበራት ወንበር ለፋሽስቶች ተላልፎ እንዳይሰጥ ለመከራከር ሲሉ ነበር የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በኢጣሊያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አንድ ልዑል መወለዱን ምክንያት በማድረግ በግራዚያኒ ትእዛዝ በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቅጽር ግቢ) በተዘጋጀው የድግስ ፕሮግራም ላይ የሚገኙ የፋሽስት ከፍተኛ ሹማምንት በሙሉ እንዲገደሉ በውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በኩል ወደ አዲስ አበባ ትእዛዝ ያስተላለፉት። [ ምንጭ፡ Campbell, I. (2007). "Yekatit" 12 Revisited: new light on the strike against Graziani. Journal of Ethiopian Studies, 40 (1/2), 135-154; Page 142] ይኽንን በፋሽስት ከፍተኛ ሹማምንት ላይ የታቀደውን የግድያ ኦፕሬሽን እንዲያስፈጽሙ የታዘዙት ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩት ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ ነበሩ። ልብ በሉ! ትእዛዙን ወደ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ በጽሑፍ የላኩት ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በጀኔቭ አብረዋቸው የነበሩት የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ናቸው። [ምንጭ፡ ዝኒ ከማሁ] ብዙ ሰው አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በፊት በዱር በገደሉ ሲንከራተቱ የነበሩ አርበኞች ይመስሉታል፤ ይህ ስህተት ነው። አብርሃ ደቦጭ ከወረራው በፊት ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ሲኖር ለጥሊያን መንግሥት ሲሰልል ተገኝቶ በሀገር ክዳት ተፈርዶበት ግራዚያኒ አዲስ አበባን እስኪቆጣጠር ድረስ በእስር ላይ የነበረ ሰው ነው። ግራዚያኒ አዲስ አበባ ሲገባ በስለላ ሲያገለግለው የነበረው የፋሽስት አገዛዝ ከእስር እንዲወጣ አድርጎት መጀመሪያ የዲቦኖ በመቀጠል የግራዚያኒ የፖለቲካ አማካሪ ኾኖ ተሾመ። ሞገስ አስገዶም ደግሞ የግራዚያኒ አስተርጓሚ የነበረ ታማኝ አገልጋይ ነበር። ሞገስና አብርሀም ንጉሠ ነገሥቱ ላቀዱት አላማ የታጩት በወዳቻቸቸው በተለይም የትምህርት ቤት ጓደኛቸው በነበረው የበጌምድሩ አርበኛ በስብሐት ጥሩነህና በሐረርጌው አማራ በስምኦን አደፈርስ ታማኝ የፋሽስት ጣሊያን ታማኝ አገልጋዮች እያሉ ነው። በዚህ ኹኔታ በስብሐት ጥሩነህ የተመለመሉት እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ፊታቸውን እየተሸፈኑ በመግባት ስለ ኦፕሬሽኑ ሥልጠና ይሰጣቸው የነበረው በመርሃቤቴው አርበኛ በደጃዝማች ለጥይበሉ ቤት ውስጥ ነበር። አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የቦንብ ጥቃት የፈጸሙ ዕለት (የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም) መነሻቸው የደጃዝማች ለጥ ይበሉ ቤት ነበር። [ምንጭ ዝኒ ከማሁ ገጽ 141] ከዚህ በተጨማሪ በግራዚያኒ ላይ የተወረወረውን ቦንብ የገዙትና ለአብርሃና ሞገስ እንዴት እንደሚፈታ አሰልጥነው የሰጧቸው ታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ ናቸው። [ምንጭ ፡ Greenfield, R. (1965). Ethiopia፡ a New Political History. FA Praeger; ገጽ 240] ደርግ ግን ንጉሡንና ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬን ማውገዝ እንጅ በባለታሪክነት መጥቀስ ስለማይፈልግ አስራ ሰባት ዓመታት ሙሉ እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን ሲያስታውስ ሲከርም በግራዚያኒ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴንና ጥቃቱን ያስፈጸሙትን ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬን ስለውለታቸው አንድም ቀን እንኳ ስማቸውን ጠርቶ በበጎ አስታውሷቸው አያውቅም። ከደርግ በኋላ የመጡት ፋሽስቶችም የቀጠሉት ደርግ በጀመረው መንገድ ነው። ልብ በሉ! ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ በግራዚያኒ ላይ ለመፈጸም ያቀዱትን ጥቃት ለማድረስ በወዳጃቸው በሰምዖን አደፍርስ አማካኝነት የመለመሏቸው አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ ቦንብ ለመጣል የታጩት በወቅቱ የግራዚያኒ የማይጠረጠሩ ታማኝ አገልጋዮችና ግራዚያኒን ከሚቀርቡ ጥቂት የተማሩ ጥቁሮች መካከል ስለነበሩ እንጂ አርበኞች ስለነበሩ አይደለም። በኦፕሬሽኑ በመሳተፋቸውም ዳጎስ ያለ ገንዘብ በደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ ተከፍሏቸዋል። ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ ከመሩ በኋላ የእረኛ ልብስ ለብሰው ራሳቸውን በመቀየር ከአዲስ አበባ ስለወጡ ሳይገደሉ የቀሩና ቀሪውን የፋሽስት የወረራ ዘመን ከነራስ አበበ አረጋይ ጋር ሆነው በአርበኛነት ሲፋለሙ የቆዩ ከግራዚያኒ የግድያ ሙከራ ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚጠቀሱ አርበኞች መካከል በሕይዎት የተረፉ ብቸኛው ሰው ናቸው። [ምንጭ: Campbell, I. (2017). The Addis Ababa Massacre: Italy's National Shame. Oxford University Press; Page 243-248.] እኒህ በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ የመሩና ያቀናበሩት አርበኛ የሕይዎት ፍጻሜ የሆነው መንግሥቱ ንዋይና ግርማሜ ንዋይ የተባሉ የሰው ደም የተጠሙና የሰው ስጋ የተራቡ አውሬዎች በ1953 ዓ.ም. በካሄዱት የአርበኞች ፍጅት ነው። ከግራዚያኒና ከሙሶሎኒ ግድያ የተረፉት ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ «ለውጥ ለማምጣት ተነሳን» ባሉ ባገራቸው ልጆች በአዛውንት እድሜ ላይ ሳሉ በማረፊያቸው ታኅሣሥ 7 ቀን 1953 ዓ.ም. ያለ ፍርድ በግፍ ተረሸኑ። ከነመንግሥቱ ንዋይ እርድ የተረፉት የደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ ጸረ ፋሽስት የትግል ጓዶች የሆኑት እነ ራስ መስፍን ስለሺና ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ደግሞ እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ያለ ፍርድ እጅ እያወጡ ፈጇቸው። ዘላለማዊ ክብር የማይጠፋ ሥራ ሰርተው ላለፉ ለአይበገሬው ጀግና ለደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ! Achamyeleh Tamiru
0 Comments
Leave a Reply. |
AuthorWrite something about yourself. No need to be fancy, just an overview. Archives
February 2022
Categories |